ሐሳብ በሁኔታዎች
ላይ ያለው ተጽዕኖ

Merhawi Fissehaye
3 min readJan 4, 2021

ቀዳሚ ክፍል

የሰው ህሊና ልክ እንደ አትክልት ጓሮ ነው፤ በጥበብ ሊተክሉበት አሊያም የአረም መፈንጫ እንዲሆን ሊተዉት ይችላሉ። ነገር ግን ቢተከልም፣ ቸል ቢባልም ፍሬዎችን ማፍራቱ ግን አይቀርም። ምንም ጠቃሚ ዘር ካልሰጡት፣ ብዙ የአረም አዝርዕት ይወድቁበታል፣ እነዚሁም እየተራቡ ዘራቸውን ያበዛሉ።

አትክልተኛ ማሳውን ከአረም እየጠበቀ፣ የሚፈልጋቸውን ፍሬዎችና አበቦች እንደሚያበቅልበት ሁሉ፣ ሰውም የህሊናውን ማሳ ከተሳሳቱ፣ ከማይጠቅሙና ንጹሕ ካልሆኑ ሐሳቦች እየጠበቀ ወደ ፍጽምና የሚያደርሱ ቀ፣ ጠቃሚና ንጹህ ሐሳቦችን መትከል ይችላል። ይህን ሂደት በመከተል በመጨረሻ ሰው የህሊናው የበላይ ጠባቂ አትክልተኛ፣ የሕይወቱ ሥራ አስፈጻሚ መሆኑን መረዳቱ አይቀርም። ብሎም በውስጡ ያለውን የሐሳቦች አሠራር እየገለጠ በየዕለቱ እየጨመረ በሚሄድ ጥራት የኃሳቦቹ ኃይልና የአመለካከቱ ዓይነት እንዴት ሕይወቱን ሁኔታዎችንና እጣፈንታውን እንደሚቀርጹ እየተረዳ ይሄዳል።

ሐሳብና ጠባይ አንድ ናቸው፤ ጠባይ በአካባቢ ሁኔታና በአጋጣሚዎች ውስጥ የሚገለጥ ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ ውጫዊ የሕይወቱ ገጽታዎች ሁሌም ከውስጣዊ ሁኔታው ጋር በጥምረት የተገናኙ ሆነው ይታያሉ። ይህ ማለት በአንድ የተወሰነ ጊዜ ላይ ያለበት ሁኔታ የአጠቃላይ ጠባዩ መገለጫ ነው ማለት ሳይሆን ሁኔታው ለጊዜው በውስጡ ካለ ለዕድገቱ ወሳኝ የሆነ አንዳች አንኳር የሆነ ሐሳብ ጋር የተገናኘ ነው ማለት ነው።

ሁሉም ሰው አንዳች ሁኔታ ውስጥ ያለው በህልውና ሕጎች ሳቢያ ነው። እዛ ቦታ ያደረሱት ወደ ጠባዩ ያሳደጋቸው ሐሳቦቹ ናቸው። የሕይወቱ ቅንብር ላይ ዕድል የሚባል ነገር ቦታ የለውም፤ ሁሉም የማይሳሳት የማይሻር ሕግ ውጤት ነው። ይህ ሕግ በዙሪያቸው ካለው ነገር ጋር ለተስማሙትም ለተጣሉትም በአንድነት ይሠራል።

የሰው ልጅ የሚያድግና ረጅም ጊዜ በሚወስድ ለውጥ ውስጥ የሚያልፍ ህልውና እንደመሆኑ አንዳች ሁኔታ ውስጥ ያለው ከሁኔታው ተምሮ እንዲያድግበት ነው፤ ስለዚህም በእያንዳንዱ አጋጣሚ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ ትምህርት ወይም ምክር ሲማር ወደሚቀጥለው አጋጣሚ ይሸጋገራል።

ሰው የውጫዊ ሁነቶች ሥሪት እንደሆነ እስካመነ ድረስ ሁልጊዜም በአጋጣሚዎች አረር መመታቱን ይቀጥላል። የፈጣሪነት ኃይል እንዳለው፣ ጠባዩ የሚበቅልባቸው አፈርና ዘሮች ላይ የማዘዝ ሥልጣን በእጁ እንደሆነ በተረዳ ጊዜ ግን የራሱ ትክክለኛ ጌታ ይሆናል።

ሁነቶች ከሐሳቦች እንደሚነሱ ማንኛውም ራስን የመግዛትና የማንጻት ልምምድ ውስጥ የነበረ ሰው ያውቃል። ምክንያቱም ውጫዊ የሕይወቱ ገጽታዎች የተለወጡት ከኃሳቡ ሁኔታ ጋር በእኩል መጠን መሆኑን ይታዘባልና ነው።

ሰው ያለማወላወል በጠባዩ ውስጥ ያሉትን ግድፈቶች ለመቅረፍ ከተጋ፣ ቅጽበታዊና የሚታይ ጉዞ ካደረገ በፍጥነት ከአንዱ አጋጣሚ ወደሌላው ይሸጋገራል።

ህሊና በስውር አንቀልባ ያዘለውን፣ የሚወደውን፣ የሚፈራውን እንኳን ሳይቀር ወደራሱ ይስባል። አቅፎ የያዘው የምኞቱ ማማ ላይ ይወጣል፣ ወዳልተገሩ የአምሮት ሸለቆዎች ይወርዳል። አጋጣሚዎች ሁሉ ህሊና የራሱ የሆነውን የሚቀበልባቸው መንገዶች ናቸው።

ህሊና ላይ የተዘራ አልያም በቸልታ እንዲያርፍ ብሎም ሥር እንዲሰድ የተፈቀደለት የሐሳብ ዘር ራሱን እያበዛ ቀስ በቀስ ወደ ተግባር ያድጋል። የራሱ የሆኑ አጋጣሚዎችንና ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። መልካም ሐሳቦች መልካም ፍሬዎችን ይሰጣሉ፣ መጥፎ ሐሳቦች መጥፎ ፍሬዎችን ይሰጣሉ። ከልብ መልካም መዝገብ፣ መልካም ነገር ይወጣል። ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉ ነገር ይወጣል እንዲል።

አፍአዊው ቁሳዊ ዓለም በውስጣዊው የሐሳብ ዓለም ልክ ይቀረጻል። ደስ የሚያሰኙም ሆነ የማያሰኙ ውጫዊ አጋጣሚዎች ለግለሰቡ ዘላቂ ጥቅም የሚመጡ ናቸው። የራሱ ማሳ ቃራሚ እንደመሆኑ ሰው በስቃይም በሐሴትም በሁለቱም ይማራል።

እንዲሰለጥኑበት የፈቀደላቸውን ውሳጣዊ ምኞቶች፣ ጉጉቶችና ሐሳቦችን በመከተል ሰው የኃሳቦቹ ፍሬዎች ፍካት ላይ ይደርሳል። ወይም በሌላ አባባል ብርሃን የሚመስሉ አሳችና ንጹህ ያልሆኑ የህሊናውን ስዕሎች በማሳደድም ሆነ ጠንካራና ከፍተኛ ጥረት ያለበት አውራጎዳና ላይ በቁርጥ ሐሳብ በመራመድ ሰው በስተመጨረሻ ኃሳቦቹ እውን ሆነው ማየቱ አይቀርም። የለውጥና የዕድገት ሕግጋት ሁሌም ግቡን ይመታል።

የቸገረው ወደ ልመና ወንጀል የሠራም ወደ ወህኒ በእጣፈንታና በአጋጣሚ ተይዞ አይመጣም፤ በደካማ ኃሳቦቹና በዘቀጡ ምኞቶቹ መንገድ እንጂ። ንጹህ ህሊና ያለው ሰውም ቢሆን በውጫዊ ኃይል ተገዶና ተጨንቆ በአጋጣሚ ወደ ወንጀል አይገባም። የወንጀል ሐሳብ በልቡ በስውር ሲቀለብ ኖሯል። እናም ምቹ ሁኔታ በተፈጠረ ሰዓት በኃሳቡ ያጠራቀመውን ኃይል በተግባር ገለጠ። ሁኔታዎች ሰውን አይሰሩትም፣ ራሳቸውን ይገልጡለታል እንጂ። ካለክፉ ዝንባሌ ወደ ክፋትና ተከትሎት ወደሚመጣው ስቃይ መውረድ አይኖርም። እንዲሁ ካለ በጎ ጉጉትና ጥረት ወደ ጽድቅም ሆነ አብሮት ወዳለ ንጹሕ ትፍሥሕት መውጣት አይቻልም። ስለዚህም ሰው የኃሳቦቹ ጌታ እንደመሆኑ የራሱ አናጢ፣ የአካባቢው ደራሲ ነው። ነፍስ በምድር ላይ በሚኖራት ጉዞም ራሷን ለመግለጥ የሚረዳትን የንጽህናዋና የጥንካሬዋ ነጸብራቅ የሆኑ አጋጣሚዎችንም ሆነ የድካሟና የእድፏ መገለጫ የሆኑ አጋጣሚዎችን ወደራሷ ትስባለች።

ሰዎች የሆኑትን እንጂ የሚፈልጉትን ወደራሳቸው የሚስቡ አይደሉም። የሆኑትን ነገር ግን ወደራሳቸው ይስባሉ። የአምሮታቸው፣ በምናባቸው የያዙት ስዕል እንዲሁም የወደፊት ፍላጎታቸው ውጤት በያንዳንዱ ደረጃ ከፊታቸው ይገጥማቸዋል። ነገር ግን ውስጣዊ ኃሳቦቻቸውና ምኞቶቻቸው የቆሸሹም ይሁኑ ንጹህ የራሳቸውን ምግብ ይመገባሉ። ዕጣፈንታችንን የሚወስነው ምስፍና በውስጣችን ነው፤ መስፍኑ እኛነታችን ራሱ ነው። ሰው የገዛ ራሱ ካቴና ነው። ሐሳብና ተግባር የእጣፈንታ ወህኒ ጠባቂዎች ናቸው። እድፋሞች ሆነው ያስራሉ። የነጻነት አማልክትም ናቸው። ንጹሐን ሆነው ነጻ ያወጣሉ። ሰው የሚገባውን እንጂ የሚመኘውንና የጸለየለትን ነገር የሚያገኝ አይደለም። ምኞትና ጸሎቱ ተገቢ መልስ የሚያገኙት ከሐሳብና ተግባሩ ጋር አብረው የሚሄዱ ሲሆኑ ብቻ ነው።

ይቀጥላል

--

--

Merhawi Fissehaye

አሳቢና ጸሓፊ ነኝ። በተለይም ኃሳብ ከሰዎች ጋር ባለው ትስስርና እንዴት ከእውነታ ጋር መገናኘት እንደሚችል መመራመር እወዳለሁ። በጽሑፎቼም እነዚህን ግኝቶቼን አሰፍራለሁ።