ሰው እንዳሰበው

Merhawi Fissehaye
3 min readOct 28, 2020

ይህ የተመስጦና የልምድ ውጤት የሆነው ትንሽ ጽሑፍ ብዙ ስለተባለለትና ስለተጻፈለት የሐሳብ ኃይል አጠቃላይ ማብራሪያ ለመሆን ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም። ከማብራራት ይልቅ መጠቆምን ግቡ ያደረገ ሥራ ነው። ዓላማውም ወንዶችና ሴቶች በሚመርጧቸውና በሚያበረታቷቸው ኃሳቦች አማካኝነት

ራሳቸው የራሳቸው ሰሪ የመሆናቸውን

እውነት ፈልገው እንዲያገኙና እንዲገነዘቡ ለማነሳሳት ነው። ሕሊና የውስጣዊው የጠባይ ልባስም ሆነ የውጫዊ የአጋጣሚዎች ካባ የሁለቱም ሸማኔ መሆኑን ለማሳየት እንዲሁም እስካሁን ድረስ ሰዎች በድንቁርናና ድካም አሹረው እንደሆነ ከዚህ ወዲህ በዕውቀትና በደስታ ይፈትሉ ዘንድ ለማድረግ ነው።

ጄምስ አለን

በጎ ኃሳቦች የገነት አምሳያ ናቸው። የውበት የግርማ የከፍታ ተምሳሌት ናቸው።
በጎ ኃሳቦች የገነት አምሳያ ናቸው። የውበት የግርማ የከፍታ ተምሳሌት ናቸው።


ሐሳብና ጠባይ

“ሰው በልቡ እንዳሰበው፣ እንደዛው ነው” የሚለው አባባል የሰውን ልጅ አጠቃላይ አኗኗርና አኳሃን የያዘ ነው። ከዛም አልፎ እያንዳንዷን የሕይወቱን አጋጣሚ መግለጽ ይችላል። በጥቅሉ የሰው ልጅ የሚያስበውን ነገር ነው። ጠባዩ ደግሞ የሚያስባቸው ሃሳቦች አጠቃላይ ድምር ነው።

ተክል ከዘር እንዲወጣ፣ ያለሱም ሊፈጠር፣ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ እንደዚሁ ደግሞ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሥራ ውስጡ ከተደበቁ የሐሳብ ዘሮች የሚመነጭ ነው፣ ያለነሱም የሚሆነውን ባልሆነ፣ የሚኖረውን ባልኖረ ነበር። ይህ እውነታ ሰው በተለምዶ “ሳላውቅ” ፣ “በደመነፍስ” ፣ “ሳላስብ” አደረግኩት ብሎ የሚሠራቸው ነገሮች ላይም ሆነ አውቆ አውጥቶና አውርዶ የሚሠራቸው ግብሮቹ ላይ በእኩል ይሠራል።

ተግባር የሐሳብ ፍካት ነው። ሐሳብ ሲፈካ የግብርን ልደት ማብሰሩ ነው። ደስታና ኃዘን ደግሞ የግብር ፍሬዎች ናቸው። ሰው ከራሱ ማሳ ላይ ጣፋጭና መራራ ፍሬዎቹን ይለቅማል።

የህሊና ሐሳብ የግብር ካብ ስቦ
በሃሳብ የኖርነው የአካል ህንጻ ክቦ
ታንጿል ተሰርቷል
ሃሳብ በሥራ ውስጥ እራሱን ይገልጣል
ክፉ ሐሳብ ይዞ የሰው ልጅ ሕሊና
ከተመላለሰ በክፋት ከጸና
ማረሻ በሬውን እንዲከተል ቅሉ
ሰውም ይገጥመዋል ክፉ ነገር ሁሉ
በበጎ ሐሳቡ በንጽሕ ከተጋ
የቀን ጥላ ሰውን ሁሌ እንደሚጠጋ
ሃሴት ይከበዋል ሲመሽም ሲነጋ

ሰው የጽኑ ሕግ ሥሪት እንጂ ሕይወቱ በማምለጥ፣ በመሸወድ፣ በመለዋወጥ፣ በሽንገላ የሚመራ አይደለም። የምክንያትና ውጤት ሕግ በቁስ አካል ዓለም ላይ ሳይሻር እንደሚጸና፣ እንደዚሁ ደግሞ በሐሳብ ዓለም ላይ ጽኑ ነው። የላቀና አምላክን የመሰለ ጠባይ በዕድል ወይም በውለታ የሚመጣ ሳይሆን ሰው በጎ ሐሳብ ለመያዝ ሲጣጣር ከአምላካዊ ጠባይ ጋር የረጅም ጊዜ ቁርኝት ሲኖረው የሚገኝ ተፈጥሯዊ ውጤት ነው። የዘቀጠና እንስሳዊ ጠባይም በተመሳሳይ የወረዱ ሐሳቦችን በስውር የማስጠጋትና የማኖር ውጤት ነው።

ሰው የራሱ ሰሪም አፍራሽም ነው። በኃሳቡ ግብአትነት ራሱን የሚያጠፋበትን መሳሪያ ይቀይሳል። እንደዚሁ ደግሞ የደስታ፣ የጥንካሬና የሰላም ሰማያዊ ቤቶችን የሚገነባበትን አካፋና ዶማ ይቀርጽበታል። በቀና ምርጫና የሐሳብን ኃይል በትትክል በመተግበር የሰው ልጅ ወደ አምላካዊ ፍጽምና ይወጣል፤ ሐሳብን በአግባቡ ባለመጠቀም ከአውሬ ደረጃ ወርዶ ይታያል። በነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል ሁሉም ዓይነት የሰው ልጅ የጠባይ ደረጃዎች ይገኛሉ። ሰሪያቸውና ጌታቸውም ሰው ነው።

በሰውነት ላይ ከሚሠሩ ማራኪ ሕግጋቶች ሁሉ ከዚህ የበለጠ አስደሳችና አበርቺ የሆነ የለም። “የሰው ልጅ የኃሳቡ ጌታ፣ የጠባዩ አናጢ፣ የሁኔታዎቹ፣ የአካባቢው፣ የዕጣፈንታው ቀራጭ ነው።” ኃይል፣ አመዛዛኝነትና ፍቅር የተሰጠው በመሆኑ፣ በኃሳቦቹም ላይ ጌታ ሆኖ በመሾሙ የሁኔታዎች ሁሉ ቁልፍ በእጁ ነው። ራሱን እንደወደደው ሊያደርግ የሚያስችሉት የደከመውን አስፈንጣሪና የታመመውን አካሚ የሆኑ ህዋሳትን በውስጡ ይዟል።

የሰው ልጅ ሁልጊዜም ጌታ ነው። በደከመና በተጣለ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ሁኖ ጌትነቱ አይለወጥም። ነገር ግን በድክመቱና በውርደቱ ጊዜ ቤቱንና ቤተሰቡን ያለአግባብ የሚገዛ ሞኝ ጌታ ይሆናል። በሁኔታው ላይ በጥልቀት ማሰብ ሲጀምርና ማንነቱ የቆመበትን ጽኑ የሕግ መሠረት በትጋት ሲፈልግ፣ ያኔ ያንን ጠቢብ ጌታ ይሆናል፣ ኃይሉን በሚዛን ይገራል፣ ኃሳቡን አስጊጦ ወደ ፍሬያማ ነገሮች ይለውጣቸዋል። ንቁ ጌታ እንደዚህ ነው። ንቁ ጌታ የውስጡን ሕግጋቶች ከተሸሸገበት የምስጢር ጓዳ አውጥቶ የገለጠና የተረዳም ነው። ይህም መገለጥ የተግባር፣ ራስን የመመርመርና የልምድ ውጤት ነው።

ወርቅና አልማዝ በከፍተኛ ፍለጋና የማዕድን ቁፋሮ እንዲገኙ፣ እንዲሁ ደግሞ ሰው የሕይወቱን እውነታዎች ፈልጎ ማግኘት የሚቻለው የነፍሱን የመዓድን ዋሻ በትጋትና በጥልቀት ሲቆፍር ነው። ይሄኔ የጠባዩ ሠሪ፣ የአኗኗሩ አናጢና የዕጣፈንታው ገንቢ መሆኑን ይረዳል። ኃሳቦቹ በራሱ ላይ፣ በሌሎች ላይ በሕይወቱና በሁኔታዎቹ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ በቅንነት እየተመለከተና እየተቆጣጠረ ከቀየረ፣ ትዕግስት በተሞላው ልምምድና ምርምር የነገሮችን ምክንያትና ውጤት ካያያዘ፣ ጥቃቅኑን እንኳን ሳይቀር የየዕለቱን አጋጣሚ ለራሱ ዕውቀትና መረዳትን፣ ጥበብና ኃይልን መቃረሚያ አድርጎ ከተጠቀመ ይህንን እውነት ያለ እንከን ያረጋግጣል። “እሹ፣ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያውን አንኳኩ፣ ይከፈትላችሁማል” የሚለው ሕግ ከሁሉ በላይ በዚህ አቅጣጫ ፍጹም ነው። የሰው ልጅ በትዕግስት፣ በልምምድና በማያቋርጥ ተማጽኖ የዕውቀት መቅደስ በር ላይ ይደርሳል።

ይቀጥላል

ቀጣይ ክፍል

--

--

Merhawi Fissehaye

አሳቢና ጸሓፊ ነኝ። በተለይም ኃሳብ ከሰዎች ጋር ባለው ትስስርና እንዴት ከእውነታ ጋር መገናኘት እንደሚችል መመራመር እወዳለሁ። በጽሑፎቼም እነዚህን ግኝቶቼን አሰፍራለሁ።